ኢትዮጵያ በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ከ3-14 ዲግሪ ሰሜን እና ከ33-48 ዲግሪ ምሥራቅ የምትገኝ አገር ስትሆን የቆዳ ስፋቱዋም 1,127,127 ካሬ ኪ.ሜ. ነው። በሰሜን ከኤርትራ፣ በምዕራብ ከሱዳን፣ በደቡብ ከኬኒያ፣ እንዲሁም በምሥራቅ ከጅቡቲ እና ከሶማሊያ ጋር ትዋሰናለች። የኢትዮጵያ አብዛኛው ግዛት በተራሮችና በሀይቆች የተሞላ ሲሆን፣ ታላቁ የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ እነዚህኑ ከፍተኛ ቦታዎች ከሰሜን ምሥራቅ ወደ ደቡብ ምዕራብ በመጋደም ለሁለት ይከፍላቸዋል። በስምጥ ሸለቆው ዙሪያም በረሃማ የሆኑ ዝቅተኛ ቦታዎች ይገኛሉ። ይኅን መሰሉ የመልክዓ-ምድር ልዩነት አገሪቷ የተለያዩ የአየር ንብረት፣ የአፈር፣ የዕፅዋት እና የሕዝብ አሰፋፈር ገጽታዎች እንዲኖራት አስችሏታል።
በከፍታና በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ዐይነት የአየር-ንብረት ክልሎች ይገኛሉ። እነሱም:-
- ደጋ - ከፍታቸው ከባሕር ጠለል 2400 ሜትር የሚጀምር እና የሙቀት መጠናቸው ከ 16 ዲግረ ሴ.ግ የማይበልጥ፤
- ወይናደጋ - ከፍታቸው ከባሕር ጠለል ከ1500 እስከ 2400 ሜትር፣ ሙቀታቸውም ከ16 ዲግረ ሴ.ግ እስከ 30 ዲግረ ሴ.ግ የሚደርስና፣
- ቆላ - ከባህር ጠለል በታች ጀምሮ እስከ 1500 ሜትር ከፍታ ያላቸው፣ የሙቀት መጠናቸውም ከ30 ዲግረ ሴ.ግ እስከ 50 ዲግረ ሴ.ግ የሚደርስ አከባቢዎች ናቸው።
ዋናው የዝናብ ወቅት ከሰኔ አጋማሽ እስከ መስከረም አጋማሽ ሲሆን፣ ከሱ ቀደም ብሎ አልፎ አልፎ የሚጥል የበልግ ዝናብ በየካቲት እና በመጋቢት ይከሰታል። የተቀሩት ወራት በአብዛኛው ደረቅ ናቸው።
No comments:
Post a Comment